‹‹ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ግብርናዉን ከመደገፍ ባለፈ የስርአተ ምግብ ለዉጥ በማምጣት የክልላችንና የሀገራችን የገቢ ምንጭ ሆኗል።›› ዶክተር ጋሻው ሙጨ
ባህርዳር ጻጉሜ 4፣ 2016 ( እ/ዓ/ሃ/ል/ጽ/ቤት)የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት በተቋሙ የሚሰሩ ተግባራትን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በክልሉ ከሚገኙ የህዝብ ግንኙነት ኣመራሮችና ባለሙያዎች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የአማራ ክልል በእንስሳት ሀብት በአገር አቀፍ ደረጃ 30% ድርሻ እንዳለው የተናገሩት የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ ዶክተር ጋሻው ሙጨ፤ ክልሉ በእንስሳት ሀብቱ ብቻ ሳይሆን በወተት ምርታማነታቸዉ የታወቁ የፎገራ ከብት፣ የአበርገሌ የፍየል ዝርያዎች፣ በስጋ ምርታቸዉ የታወቁ የዋሸራ በግ ዝርያዎች፣ በስጋ ምርታቸዉ የታወቁ የቲሊሊ የዶሮ ዝርያዎች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
የክልሉን ህዝብ የዘርፉ ተጠቃሚ ለማድረግ ዘርፈ ቡዙ ተግባራት መከናዎናቸዉን አክለው የገለጹት ሃላፊው፤ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ግብርናዉን ከመደገፍ ባለፈ የስርአተ ምግብ ለዉጥ በማምጣት የክልላችንና የሀገራችን የገቢ ምንጭ ሆኗል ብለዋል፡፡
ዘርፉን የመኖ አቅርቦት ችግር፣ የመሰረተ ልማት ችግር፣ የገበያ ትስስር፣ ኃላቀር የሆነ ልማዳዊ የአረባብ ዘዴ፣ የእንስሳት በሽታዎች እና የዝርያ አለመሻሻል እየፈተኑት ነዉ ያሉት ሃላፊዉ፤ በቀጣይ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የመላ ማህበረሰቡና የባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዳለ ሆኖ በተቋሙ የሚሰሩ ተግባራትን ለማህበረሰቡ በማስተላለፍ በኩል የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግስ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው በበኩላቸው፤ ክልላችን ወደ ተሻለ እድገትና ብልፅግና ለማሸጋገር እና ህዝባችን ያለውን ሃብት በአግባቡ ተጠቅሞ ከድህነትና ከልመና እንዲወጣ በሁሉም ተቋማት የተሰሩ ተግባራትን በአግባቡ ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
እንደ ህዝብ፣ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ሃላፊነታችን በሙያው ለማገዝና በዘርፉ የሚሰሩ ባለሃብቶችን ለመሳብ ተቋሙ በእንስሳትና ዓሳ ሃብቱ ልማት እየሰራ ያለውን ተግባር በሁሉም የሚዲያ ዓይነቶች ለህዝብ ማሳወቅ ይኖርብናል ሲሉ ዶክተር መንገሻ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ከመድረኩ ተሳታዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቆዎች ተነስተው ምላሽ የተሰጣቸው ሲሆን በምክክር መድረኩ የሚመለከታቸው ተቋማት አመራሮች፣ የሁሉም ተቋማት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች እና የሚዲያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡