ዜና  

የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሣ ሃብት ዘርፍ ልማት ፕሮጀክትና ማህበራት በዶሮ እርባታ፣ በቀይ ስጋ ፣ በወተትና በዓሣ ሃብት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ማህበራት ውጤታማነትን አስመልክቶ ምክክር አካሂደዋል፡፡

የምክክሩ ዓላማ በእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት ስራቸውን በእቅድ እንዲመሩ ማስቻል፤ ከሸማቹ የገበያ ትስስር መፍጠር ፣ የተሻለ ጥራት ያለው ምርት እንዲያመርቱ ማስቻልና መደገፍ እንደሆነ የአማራ ክልል የኀብረት ስራ ማስፋፊያ ኤጀንሲ ኃላፊ ኃይለልዑል ተስፋ ተናግረዋል፡፡

“አምራችና ሸማች ጥብቅ ትስስር መፍጠራቸው ለሀገር እድገት መሰረት ነው” ያሉት ኃላፊው ሁለቱ አካላት ትስስር የማይፈጥሩ ከሆነ ተጠቃሚ የሚሆነው ሕገ ወጥ ደላላው ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ሸማቹ የሚፈልገው የምርት ጥራት ፣አይነት፣ብዛትና ጊዜን በአግባቡ መረዳት አምራቹን ስኬታማ ያደርጋል፤ ለዚህም በየወቅቱ መነጋገር እንደሚያስፈልግ አቶ ኃይለልዑል አስገንዝበዋል፡፡

የወተት ልማት ምርት ሸማቿ ወይዘሪት እልልታ ካሳ ውይይቱ ገዢና ሻጭን የበለጠ ሊያቀራርብ ይችላል ብላለች፡፡ በተለይ ገዢው ከየትኛው ሸማች መግዛት እንዳለበት አማራጮች እንዲኖሩት ያስችላልም ነው ያለችው፡፡

አቶ ዘየነው ዓለሙ የአውራምባ ማህበረሰብ የገበሬዎችና እደ ጥበባት ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበራት ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ማህበራት ውጤታማ እንዲሆኑ የገበያ ትስስሩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ዘርፍ ኘሮጀክት በክልሉ በእንስሳት ሃብት ልማት ለተሰማሩ ማህበራት ድጋፍ ከሚያደርጉ ኘሮጀክቶች ውስጥ አንዱ መሆኑን የአማራ ክልል እንስባት ሃብት ልማት ኤጀንሲ ማስፊፊያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዳዊት ገዳሙ አስረድተዋል፡፡

ኘሮጀክቱ በክልሉ በ15 ወረዳዎች የሚንቀሳቀስ ሲሆን በዶሮ ሃብት ልማት፣ በቀይ ስጋ፣ በወተትና በዓሣ ሃብት ልማት ላይ ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ማህበራት ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አቶ ዳዊት ተናግረዋል፡፡ ማህበራቱ በተሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ኤጀንሲው የቴክኒክና ሙያ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የተደራጁ ማህበራት ለማጠናከር የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ማድረግ ፣ የተሻለ መኖን ማቅረብና ጤንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን መስራት ኤጀንሲው ከኘሮጀክቶች ጋር የሚያከናውነው ተግባራት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ኘሮጀክቱ በ2ዐ12 ዓ.ም.በአማራ ክልል በ15 ወረዳዎች 1ሺ 35ዐ የጋራ ፍላጐት ቡድን አቅፎ ነበር ስራውን የጀመረው፤ ከነዚህ ውስጥ የተሻለ ፈአፃፀም ያሳዩ 31 ቡድኖች ወደ ደረጃ ሁለት ማህበር ተሸጋጋረዋል ብለዋል፡፡ ወደ ደረጃ ሁለት ለተሻጋገሩ ማህበራት ለእያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም አቶ ዳዊት አስረድተዋል፡፡

በስራ አፈፃፀማቸው ለተመረጡ ማህበራት ድጋፍ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከሸማቹ ጋርም በማቀራረብ የገበያ ትስስር በሚፈጠርባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡

በእንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ከ2ዐ12 ዓ/ም ጀምሮ በውስን ሃብትና መሬት በርካታ የክልሉ ዜጐችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አቶ ዳዊት አመልክተዋል፡፡

በዚህ ኘሮጀክት ብቻ ከ2ዐ ሽህ በላይ ዜጐች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ነው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ያብራሩት፡፡

LOADING
Photo Title 1Photo Title 2Photo Title 3Photo Title 4Photo Title 5

download

 

 

Copyright©2022-ANRS Livestock Resources Development & Promotion Agency. All rights reserved! |